የአፋር ልማት ማህበር ከበአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ስድስት ተጨማሪ ክፍሎች ማስፋፋያ ግንባታ የተደረገለት አሰቦዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስመረቁ።
በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አብዱ ሙሳ ገለጹ። የአፋር ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ኮንቴ ሙሳ (ዶ/ር) እንዳሉት ማህበሩ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ነው። በቀጣይም ማህበሩ በተለይም በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የክፍል ጥበት ችግርን ለመቅረፍ ድጋፉን ይቀጥላል ብለዋል። ከዚህ ቀደም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ዱብቲ፣ ሎጊያና ሠመራ ድረስ ተጉዘው ይማሩ እንደነበር የገለፀችው ተማሪ ሞሚና ዓሊ ናት። የተጨማሪ ክፍሎቹ መገንባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በቅርበት እንድታገኝ የሚያስችላት በመሆኑ ደስታዋን ገልጻለች። በሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ስድስት ተጨማሪ ክፍሎች ማስፋፋያ ግንባታ የተደረገለት አሰቦዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ፤ በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ ነው። በዚህም መሠረት ዛሬ ስድስት ተጨማሪ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልሃዱ ኮሎይታ በበኩላቸው የተደረገውን ማስፋፊያ ተከትሎ በትምህርት ቤቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መስጠት ይጀመራል ብለዋል። የተጨማሪ ብሎክ መገንባት በቀጣይነት ለምናከናውነው ስራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉት ሃላፊው ማህበረሰቡ በራሱ አቅም ትምህርት ቤቱን ማገዝና መንከባከብ እንዳለበት አሳስበዋል። በምረቃ ሰነ-ስርዓቱ ላይ የአፋር ልማት ማህበር እና የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። ሰመራ፤ ሚያዝያ 18/2017






